የድረሱልን ጥሪ

የድረሱልን ጥሪ!!!

 

 በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ ሀገራት በሚመጡ የትምህርት ዕድሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች መምህራንን እንዲሁም ከሳይንስና ኢኖቬሺን ተማሪዎችን እየመለመለ እንደሚያስተምር ይታወቃል። መምህራኑ እና ተማሪዎቹ ለትምህርት ሲላኩ ከሚሰሩበት ተቋም ጋር ህጋዊ ዉል ይዘዉ ደሞወዛቸዉም በየወሩ እንደሚከፈል ተፈራርመዉ ነዉ።

 

በሩሲያ ሀገርም የሩስያ መንግስት የሚሰጠዉን ነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሆነን ትምህርታችን በመከታተል ላይ ያለን  ተማሪዎች እንገኛለን ።

 

ነገር ግን በየጊዜዉ ችግር ላይ እንደሆንን እና የሚከፈለንም ክፍያ በቂ አለመሆኑን በጥናት የተደገፈ ማስረጃ ለሚመለከተዉ አካል የላክን ቢሆንም ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለን ቆይተናል።

 

በየወሩ የሚከፈለን ደሞዝ ለዶርምተሪ ክፍያ፣ለጤና መድህን፣ለቪዛ እድሳት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ለመግዛት፣ ለምግብ የሚዉል ነዉ ።ይህም ሶስተኛ ዲግሪ በመስራት ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች በየጊዜዉ ለጥናትና ምርምር የሚወጣዉን ሳይጨምር ማለት ነዉ።በመሆኑም በሚሰጠን ደሞዝ ወር እስከወር መድረስ እያቃተን በችግርና በብድር ነዉ የምንደርሰዉ።

 

ችግራችን የከፋ የሚያደርገዉ ከነዚሁም ገንዘብ ወሩን ጠብቆ አለመላኩ ነዉ ። በተደጋጋሚ ለሚመለከተዉ አካል በደብዳቤም በስልክም ብናሳዉቅም በማናለብኝነት በስንት ጩኸት እና ለቅሶ አራት እና አምስት ወር አዘግይቶ መላኩን ተያይዘዉታል ።

 

 በተደጋጋሚ ቅሬታ ስናቀርብ ፖለቲካዊ መልስ መስጠት የማይታክተዉ አካል አሁን ደሞ ገንዘብ የመላኪያ አማራጭ የለንም የሚል አሳማኝ ያልሆነ መልስ ቢሰጥም አሁንም አማራጮችን ከመጠቆም አላረፍንም። ከመሰረቱም ችግሩን ችላ የማለት እንጂ ገንዘቡ ሊከፈለን የሚገባው አሁን ያለዉ ወቅታዊ ክስተት ከመጀመሩ ከ3 ወራት በፊት ነበር።

 

የሌሎች ሀገራት ተማሪዎች የእኛን አይነት ችግር ባይኖርባቸዉም አሁን ባለዉ ወቅታዊ ሁኔታ የስነልቦና ቀዉስ እንዳይደርስባቸዉ የተለየ ክትትል እያደረጉላቸዉ ሲሆን ክፍያቸዉንም ባሉት አማራጮች ተጠቅመዉ ወቅቱን ጠብቀዉ እየላኩ እንደሆነ እያየን ነዉ ።እኛ ግን በክብር ከምንኖርበት ከሞቀ ጎጇችን አብዛኞቻችንም ልጆቻችን ቤተሰቦቻችን በትነን የመጣነዉ ነገ ለሀገርም ፣ለምንሰራበት ተቋምም የተሻለ ልምድ እና ዕዉቀት ይዘን ለመመለስ ቢሆንም አሁን ግን እንደ ሀገር አልባ፣ እንደ የሚቆረቆርለት አካል እና መንግስት እንደሌለዉ ፣በህጋዊ መንገድ ህጋዊ ዉል ይዞ እንዳልመጣ ምናምንቴ ተቆጥረናል።

 

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚያስፈልገው ነገር ሁኔታዎች ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሄደው ከሀገር ለቃችሁ ውጡ ብንባል እንኳን ሀገር ከተማ የምንለቅበት ገንዘብ እጃችን ላይ አለመኖሩን ነው ። እንኳን በሰው ሀገር ይሄ ሁሉ ችግር ባለበት የ5 ወር ደሞወዝ ሳይከፈል ሀገር ቤት እንኳን የአንድ ወር ደመወዝ ሳይከፈል መኖር ምን ያህል የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ግልፅ ነዉ ።

 

ስለሆነም መንግስት ባፋጣኝ ገንዘቡን ይላክልን፣ከፍተኛ ችግር ላይ ነን። በተለያየ ጊዜ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት የተወሰነ ጊዜ እየታገስን የቆየን ቢሆንም አሁን ግን እኛን የሚረዳን አካል ባለመኖሩ ሁሉም ነገር ከአቅማችን በላይ ሆኗል ...ከዚህ በኋላም ወሩን አንድ ቀን እንኳን አሳልፎ የሚመጣ ክፍያን የማንታገስ ሲሆን መንግስት ይሄን ማድረግ ካልቻለ ወደ ሀገራችን በሰላም ይመልሰን ተምረን ለሀገር ባንተርፍ ለቤተሰቦቻችን ግን መኖራችን ግድ ነውና ...

 

በመሆኑም ድረሱልን የሚሰማ አካል ካለ ችግራችን ከእኛ አቅም በላይ ስለሆነ ድምፃችን አሰሙልን እንላለን። 

 

በሩስያ ሀገር የመጀመሪያ ፣ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታችንን እየተከታተልን ያለን ተማሪዎች


በሩስያ ሀገር የመጀመሪያ ፣ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች    Contact the author of the petition